Monday, October 22, 2012

የልጆቹን እናት በጥይት ደብድቦ ገድሏል የተባለው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ

-    የሟች እናትና ሁለት ግለሰቦች ቆስለው መትረፋቸው ታውቋል

በታምሩ ጽጌ

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከኦሎምፒያ ወደ መስቀል ፍላወር በሚወስደው መንገድ፣ ላፓሪዚያን ካፌ ፊት ለፊት ቅዳሜ ከጠዋቱ 2፡15 ሰዓት ላይ የልጆቹን እናት በጥይት ደብድቦ ገድሏል የተባለው ግለሰብ፣ እዚያው በቁጥጥር ሥር መዋሉን በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ ‹‹እሷም ልጆቼም ጠልተውኛል›› በሚል ተስፋ ቆርጦ ዕርምጃውን ለመውሰድ እንደወሰነ ሲናገር ተደምጧል የተባለው ተጠርጣሪ፣ ግለሰቧን ለመግደል በተኮሳቸው ጥይቶች አብረዋት የነበሩትን እናቷንና በአካባቢው ላይ የነበሩ ሁለት ግለሰቦችን ማቁሰሉን የዓይን እማኞቹ ተናግረዋል፡፡

ሰሞኑን ይከፈታል በተባለው ካርቱም ሬስቶራንት መግቢያ በር አጠገብ ቶዮታ ኮሮላ እያሽከረከረች ወደ መስቀል ፍላወር አቅጣጫ ትጓዝ የነበረችን አንዲት ሴት፣ ሀችባክ የሚያሽከረክር አንድ ግለሰብ ከፊት ለፊቷ ቀድሞ መንገዱን በመዝጋት እንዳስቆማት የዓይን እማኞቹ አስረድተዋል፡፡

ከፊቷ የቆመውን ተሽከርካሪ እንዳየች በድንጋጤ ፍሬን የያዘችው ሟች፣ የልጆቿ አባትና የቀድሞ ባለቤቷ መሆኑን እንዳወቀች የመኪናዋን በር ከፍታ ለመውጣት በሩን ስትታገል፣ ግለሰቡ ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ይዞ በመውረድ ከመኪናዋ ሳትወርድ ውስጥ ያለውን ጥይት ሙሉ በሙሉ እንዳርከፈከፈባት፣ የተመታችውም በሆዷ አካባቢና አንገቷ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪው የልጆቿ እናት መሞቷን ካረጋገጠ በኋላ ራሱን ለመግደል የያዘውን ክላሽ ወደራሱ ቢስበውም ጥይት በመጨረሱ ተርፏል፡፡

የዓይን እማኞቹ ሁለቱን ግለሰቦች ከሚያውቁና በአካባቢው ከተገኙ ሰዎች እንደሰሙት ተጠርጣሪው ባለሀብት መሆኑን፣ ከሟች ሁለት ልጆች እንደወለደና ባለመስማማታቸው ንብረታቸውን ተከፋፍለው ተለያይተዋል፡፡

ሟች ሌላ ትዳር ይዛ አንድ ልጅ መውለዷንም እንደሰሙ እማኞቹ ገልጸዋል፡፡ የዓይን እማኞቹ አደጋው በደረሰበት ቦታ ላይ ከነበሩና ሁለቱን ግለሰቦች ከሚያውቁ ሰዎች እንደሰሙት ከሆነ፣ ተጠርጣሪው ከሟች በወለዷቸው ሕፃናት ላይም አደጋ ሳያደርስ አይቀርም የሚል ሥጋት አለ፡፡

አደጋው የተከሰተው በርካታ ሰዎች በሚሰበሰቡበት ደንበል ሲቲ ሴንተር አካባቢ መስቀለኛ መንገድ አጠገብ በመሆኑ፣ የፌዴራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረቦች ፈጥነው በመድረስ ቦታውን በመዝጋታቸው፣ በቦታው የነበሩ የዓይን እማኞች ክስተቱን እስከ መጨረሻው መከታተል አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው ከተገኙት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሰው መግደል ወንጀል ዲቪዚዮን ባልደረቦች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሊሳካልን አልቻለም፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment