Friday, August 17, 2012

ምንልክ ተጕዞ የምትጠይቁኝ፡ ፊትም ኣላለፈ፡ ኋላም ኣይገኝ።መልካም ልደት ለእምዬ ምኒሊክ


ምንሊክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፡
ግብሩ ንቊላል ነበር ይህን ግዜ ኣበሻ።
በሠራው ወጨፎ፡ ባመጣው ርሳስ፡
ተፈጠመ ጣልያን፡ ኣበሻ ንዳይደርስ።
 
ምንልክ ተጕዞ የምትጠይቁኝ፡
ፊትም ኣላለፈ፡ ኋላም ኣይገኝ።
ኣባተ በመድፉ ኣምሳውን ሲገድል፡
ባልቻ በመትረየስ ነጥሎ ሲጥል፡
የጎጃሙ ንጉሥ ግፋ ብሎ ሲል።
ቴጌ ጣይቱ ቴጌ ብርሃን፡
ዳዊትዋን ዘርግታ ስምዓኒ ስትል።
ተማራኪው ባዙቅ ውሃ ውሃ ሲል፡
ዳኛው ስጠው ኣለ ሠላሳ በርሜል።
ንደ በላዔ ስብዕ እንደመቤታችን፡
ሲቻለው ይምራል የኛማ ጌታችን።
ተብሎላቸዋል እምዬ ምኒሊክ::ንጉስ ምኒሊክ ሁለተኛ ሳህለማርያም ተብለው ከንጉስ ተክለሃይማኖት እና ወይዘሮ እጅጋየሁ በዛሬዋ ቀን በ1884 ነበር የተወለዱት፡፡በሰባት አመታቸው የአፄ ቴውድሮስ ምርኮ ሆነው ወደ መቅደላ ተጋዙ፡፡ከዘጠኝ አመታት የግዞት ቆይታ የተገላገሉት የእናታቸው ታማኞች ከመቅደላ በማሸሻቸው ነበር፡፡ለ12 አመታት በሸዋ ንጉስ ነበሩ፡፡አፄ ዮሃንስ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ተብለው ሲቀቡ እርሳቸው አንድ ደረጃ ዝቅ ብለው በሸዋ ንጉስነታቸው ቀጥለዋል፡፡
ዶ/ር ስርግው ሃብለ ስላሴ ዳግማዊ ምኒሊክ-የአዲሱ ስልጣኔ መስራች በሚለው መፅሃፋቸው መግቢያ ስለ አፄ ምኒሊክ እንዲህ ይላሉ፡፡
“አፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ድርጊቶች የተከሰቱበት ነው፡፡ከእነዚህም በአፄ ቴውድሮስ ዘመነ መንግስት ጀመረው ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ተልዕኮ የተጠናቀቀበት አንዱ ሲሆን ሌላው ደግሞ ዘመናዊ ስልጣኔ ወደ ኢትዮጵያ የገባበት ነው፡፡እነዚህ ሁለቱን ያስተሳሰራቸው እና ያጠናከራቸው ሌላ ታላቅ ድርጊት አለ፡፡እርሱም የአድዋው ድል ነው፡፡እርሱ ባይታከልበት ኖሮ የአንድነቱ ህንፃ ይፈራርስ ነበር፡፡የስልጣኔውም መንገድ አቅጣጫውን ይስት ነበር፡፡ሁለተኛው ድርጊት ለዘመናዊ ስጣኔ መጀመር የአዲስ አበባ መመስረት ወሳኝ ሚና ተጫውቷል፡፡ለረጅም ዘመን ተንሰራፍቶ የኖረው ብቸኛ ኖሮ ተወግዶ አገሪቱ ከአለም ህብረተሰብ ተቀላቅላ አዲሱን ስልጣኔ ለመቋደስ እጇን ዘረጋች፡፡ይህም ሊሆን የቻለው በዳግማዊ ምኒሊክ ያልጠቆጠበ ጥረት እና ትጋት ነበር፡፡”

ኢትዮጵያ ሃኪም ቤት፤ዘመናዊ ትምህርት ቤት፤የመብራት ሃይል፤ውሃ፤ፖስታ፤ስልክ እና ቴሌግራፍ፤አውቶሞቦል ብስክሌት እና ካሚንን ያወቀችው በአፄ ምኒሊክ ብልህ አመራር ነበር፡፡የባቡር ጥንስስ ሀ የተባለውም በእርሳቸው ዘመነ መንግስት ነው፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመንግሥት ማተሚያ ቤት የተቋቋመው በአፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን፣ ጊዜውም በ1899 ዓ.ም ነበር፡፡ የማተሚያ ቤቱ መቋቋም ዋናው ዓላማ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የአማርኛ ጋዜጣ የሆነው ‹‹አዕምሮ›› የተሰኘ ጋዜጣን ለማተም ነበር፡፡ ሌላው የማተሚያ ቤቱ መቋቋም ዓላማ ለቢሮ መገልገያ የሚውሉ የተለያዩ ካርኒዎች ፣ ደረሰኞች፣ መዛግብትና የጽሕፈት መሣሪዎችን ለማተም ነው፡፡ በዚህ ወቅት ማተሚያ ቤቱ የተለያዩ ስያሜዎች እንደነበሩት የታሪክ መዛግብት ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህም፡-
1. የኢትዮጵያ ማተሚያ ቤት
2. የመንግሥት ማተሚያ ቤት
3. መርሃጥበብ ማተሚያ ቤት ናቸው፡፡
የመጀመሪያው የአማርኛ ጋዜጣ ‹‹አዕምሮ›› የተቋቋመው ሙሴ ኢንዲሪያሰ ካቫዲ በሚባል ግሪካዊ ነጋዴ ነበር፡፡ አፄ ምኒሊክ አዕምሮ የሚል ስያሜ የሠጡት ይህ ሣምንታዊ ጋዜጣ ህትመት ከመጀመሩ በፊት 24 የሚደርሱ ቅጅዎች በእጅ እየተፃፉ ለአፄ ምኒሊክና ለሹማሚንቱ ይታደል እንደነበር ይነገራል፡፡ የታዘዘው የህትመት መሣሪያ አዲስ አበባ ገብቶ መርሃጥበብ ከተተከለ ከጥቂት ወራት በኃላ ፣ የጋዜጣው ቅጅ ከ24 ወደ 200 ከፍ ማለት ጀመረ፡፡ ይህን የተገነዘቡት ንጉሡ (አፄ ምኒሊክ) ደስታ ስለፈጠረላቸው ሌላ አዲስ ማተሚያ ማሽን ከአውሮፖ ለማስገባት ቃል ገቡ ፡፡ ይሁን እንጂ የጋዜጣው ህትመት 1903 ዓ.ም ተቋረጠ ፡፡ የጋዜጣው ህትመት እንደገና በ1907 ዓ.ም ቢጀምርም፣ በወቅቱ የኢትዮጵያና የጀርመን ግንኙነት በጥሩ ሁኔታ ላይ ስላልነበረና የጋዜጣው አዘጋጅ አፍቃሬ ጀርመን ስለነበረ፣ የጋዜጣው ህትመት በኢትዮጵያ መንግስት ትዕዛዝ በ1909 ዓ.ም እንዲቋረጥ ተደረገ፡፡
ከ1881-1985 ድረስ ኢትዮጵያን የገዙት አፄ ምኒሊክ ወደ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ባህርዛፍን ከአውስትራሊያ ወደ ኢትዮጵያ አስገቡ፡፡
አፄ ምኒሊክ በሚኒስትሮች ደረጃ የተዋቀረ የአስተዳደር ስርዓት ዘርግተውም ነበር፡፡አፈ ንጉስ ነሲቡ የፍትህ ሚኒስትር፤ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ የጦር ሚኒስትር ሆነው ካገለገሉ ሰዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
እምዬ ምኒሊክ በፈረስ ስማቸው አባ ዳኘው እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ነገስታት ሁሉ የዚችን ሃገር ዳር ድንበር ለማስከበር ደፋ ቀና ሲሉ ኖረዋል፡፡በዚህም ስኬታማ ነበሩ፡፡ከሌሎች ነገስታት አንፃር በዘመነ መንግስታቸው በተለይም ከአድዋ ድል በኋላ በነበራቸው ሰላም ይህችን ሃገር ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ለማስተዋወቅ ሞክረዋል፡፡ሙከራቸውም ፍሬያማ ነበር፡፡
መልካም ልደት(ከተባለ ከዚህ አለም በሞት ለተለየ ሰው) ለእምዬ ምኒሊክ

No comments:

Post a Comment